BOSAD ስለ አጥንት ጤና፣ ስለ ጉዳትና የአጥንት ስብራት ሕክምና፣ ስለ ማገገምና ስለ አጥንትና ጡንቻ ሥርዓት ምርምር ትክክለኛ፣ ለሁሉም ተደራሽና በኃላፊነት የተዘጋጁ መረጃዎችን ለማቅረብ ይሠራል።

ይህ ፖሊሲ በBOSAD ዲጂታል መድረኮች ላይ የሚቀርቡ መረጃዎችን ለማዘጋጀት፣ ለመገምገም፣ ለማተምና ወቅታዊነታቸውን ለመጠበቅ የሚከተሉትን መርሆዎች ያስቀምጣል።

1. የይዘት አዘገጃጀት መርሆዎቻችን

BOSAD ለሕዝብ መረጃ ሲያዘጋጅና ሲያቀርብ የሚከተሉትን አምስት መርሆዎች ይከተላል።

ትክክለኛነት

መረጃዎች በእውነታ ላይ የተመሠረቱ፣ በተገቢ ማስረጃዎች የተደገፉና ያለ ማጋነን ወይም ማዛባት የቀረቡ መሆን አለባቸው። የሳይንሳዊ ምርምር ግኝቶችና የሕክምና መረጃዎች በወቅቱ ያለውን ሳይንሳዊ ዕውቀትና ዕውቀቱ የተገኘበትን ሁኔታ በትክክል ማንጸባረቅ አለባቸው።

ግልጽነት

መረጃዎች ለታለመላቸው አንባቢዎች በቀላሉ የሚገቡ መሆን አለባቸው። አስፈላጊ ሲሆን ልዩ የሙያ ቃላት በቀላል ቋንቋ ይብራራሉ። የመረጃዎቹ አደረጃጀትና አቀራረብም ሳይንሳዊ ትክክለኛነታቸውን ሳይቀይር ለመረዳት የሚያመች መሆን አለበት።

ግልጽ አሠራር

የሳይንሳዊ መረጃዎች ምንጭና የተገኙበት አውድ ግልጽ መሆን አለበት። የምርምር ጸሐፊዎች፣ የገንዘብ ድጋፍ ምንጮች፣ የተሳታፊ ተቋማት ግንኙነቶችና የምርምሩ ዋና ዋና ውስንነቶች ከሚመለከታቸው ሥራዎች ጋር ተያይዘው ይገለጻሉ።

ተገቢነት

ይዘቶች የታካሚዎችን፣ የቤተሰቦችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የአስተማሪዎችን፣ የተመራማሪዎችንና የተቋማትን ፍላጎቶች ከግምት በማስገባት ይዘጋጃሉ። የመረጃዎቹ ዝርዝር መጠንና አቀራረብ ለታለመላቸው አንባቢዎችና ለትምህርታዊ ዓላማቸው ተስማሚ መሆን አለበት።

ኃላፊነት

መረጃዎች ሲዘጋጁ የታካሚዎች ደህንነትና ግላዊነት፣ የማኅበረሰቡ ባህላዊ ሁኔታ እንዲሁም መረጃው በተሳሳተ መንገድ ቢተረጎም ወይም አላግባብ ቢጠቀሙበት ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት በጥንቃቄ ከግምት ውስጥ ይገባል።

2. የመረጃ ምንጮችና ሳይንሳዊ ማስረጃዎች

BOSAD መረጃዎቹን ሲያዘጋጅ በባለሙያዎች የተገመገሙ ሳይንሳዊ ጥናቶችን፣ እውቅና ያላቸውን የሕክምና መመሪያዎች፣ ታማኝ የሕዝብ ጤና መረጃዎችንና አስፈላጊ የተቋማት ሕትመቶችን እንደ ምንጭ ይጠቀማል።

የመረጃ ምንጮች ተዓማኒነታቸው፣ ሳይንሳዊ ጥራታቸው፣ ለርዕሱ ያላቸው አግባብነትና ለሚዘጋጀው ይዘት ተስማሚ መሆናቸው ይገመገማል።

የምርምር ግኝቶች ሲቀርቡ የጥናቱ ዓይነትና ንድፍ፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ የተካሄደበት ሁኔታ፣ የምርምር ዘዴዎችና ውስንነቶች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። በተወሰነ የጥናት ቡድን ላይ የተገኙ ውጤቶች ማስረጃው ከሚደግፈው በላይ በማስፋት ለሁሉም ሰዎች ተፈጻሚ እንደሆኑ አይቀርቡም።

በሁለት ነገሮች መካከል የታየ ግንኙነትን ከተረጋገጠ የምክንያትና የውጤት ግንኙነት እንለያለን። እንዲሁም በማስረጃ የተረጋገጡ ግኝቶችን፣ የሳይንሳዊ ትርጓሜዎችንና ገና ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለይተን እናቀርባለን።

ማስረጃዎች ውስን፣ ያልተሟሉ ወይም እየተለወጡ ባሉበት ጊዜ እነዚህ ውስንነቶች በይዘቱ ውስጥ በግልጽ ይገለጻሉ። አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶች ወይም አስፈላጊ ለውጦች ሲኖሩ የትምህርት መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ ይሻሻላሉ።

በምርምር መዝገቦች ውስጥ የሳይንሳዊ ሕትመቶች ዋና ርዕሶች፣ የጸሐፊዎች ስሞች፣ የማጣቀሻ መረጃዎች፣ DOI መለያዎችና የምንጭ አገናኞች እንደ መጀመሪያው ይጠበቃሉ። የምርምር ማጠቃለያዎች ደግሞ የዋናውን ጥናት ትርጉም ሳይለውጡ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለአንባቢዎች ይበልጥ ግልጽና ተደራሽ ያደርጋሉ።

3. የይዘት ግምገማና ሕትመት

BOSAD እንደ ይዘቱ ዓይነት፣ እንደ ታለመለት ተጠቃሚና እንደ አጠቃቀሙ ሁኔታ ተገቢ የሆኑ የይዘት አዘገጃጀትና የግምገማ መስፈርቶችን ይከተላል።

የጤና መረጃዎች

የጤና መረጃዎች ከመታተማቸው በፊት ትክክለኛነታቸው፣ ግልጽነታቸው፣ ለርዕሱ ያላቸው ተገቢነትና ከሳይንሳዊ ማስረጃዎች ጋር ያላቸው ወጥነት ይገመገማሉ።

በሕክምናዊ ግምገማው ወቅት የታካሚዎች ደህንነት፣ የመረጃው ዓላማ እንዲሁም ለአጠቃላይ ትምህርት የሚቀርብ መረጃ ከግለሰብ የጤና ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከሚሰጥ የሕክምና ምክር የሚለይበት ሁኔታ ከግምት ውስጥ ይገባል።

የምርምር መረጃና መዝገቦች

የጥናት መግለጫዎች፣ የሳይንሳዊ ሕትመት መዝገቦችና የምርምር ማጠቃለያዎች የመጀመሪያውን ሳይንሳዊ ሥራ በትክክል በሚያንጸባርቅ መንገድ ይዘጋጃሉ።

በተለይም ለምርምሩ ጥያቄ፣ ለተጠቀሙባቸው የምርምር ዘዴዎች፣ ለጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ለተካሄደበት ሁኔታ፣ ለውጤቶቹ፣ ለውስንነቶቹና ለደጋፊ የመረጃ ምንጮች ተገቢው ትኩረት ይሰጣል።

የምርምር ጸሐፊዎች ስሞች፣ የሕትመት መረጃዎችና የመጀመሪያው ምርምር መለያዎች እንደ ዋናው ምንጭ ይጠበቃሉ።

የሙያ ትምህርት

ለጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡ መረጃዎች፣ የመማሪያ ጉዳዮችና ተግባራዊ የትምህርት መርጃዎች ለታለመላቸው ተጠቃሚዎችና ለትምህርታዊ ዓላማቸው ተስማሚ ሆነው ይዘጋጃሉ።

የሕክምና ሂደቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችና ተግባራዊ የማሳያ መርጃዎች ተገቢ የሆነ ሥልጠናና የባለሙያ ክትትል ባለበት አውድ ውስጥ ይቀርባሉ።

ለባለሙያዎች የሚዘጋጁ የትምህርት መርጃዎች ለመማርና ለሕክምናዊ ውይይት የሚያግዙ ቢሆኑም፣ የሙያ ልምድን፣ ተገቢ የሕክምና መመሪያዎችን ወይም በእያንዳንዱ ታካሚ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የባለሙያ ውሳኔን አይተኩም።

የይዘት አዘገጃጀትና የሕክምና ግምገማ ኃላፊነቶች

የይዘት አዘገጃጀት ግምገማ የመረጃዎችን ግልጽነት፣ ወጥነት፣ የምንጮች ተዓማኒነት፣ አቀራረብና ከBOSAD የሕትመት መስፈርቶች ጋር ያላቸውን ተስማሚነት ይመለከታል።

የሕክምና ግምገማ ደግሞ የመረጃዎችን ሕክምናዊ ትክክለኛነት፣ ደህንነትና ለታለመላቸው አጠቃቀም ተገቢ መሆናቸውን ያረጋግጣል።

የግምገማው ዓይነትና ጥልቀት እንደ ይዘቱ ባህሪና ዓላማ ይለያያል።

4. ቋንቋና የመረጃ ተደራሽነት

BOSAD የተለያዩ ተጠቃሚዎች መረጃ እንዲያገኙ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች መረጃዎችን ያቀርባል።

ትርጉሞች የመጀመሪያውን ይዘት ትርጉም በትክክል የሚያስተላልፉ ሲሆኑ፣ በሚተረጎሙበት ቋንቋ ተፈጥሯዊ የሆኑ አገላለጾችንና ተገቢ የሙያ ቃላትን መጠቀም አለባቸው።

በተለይም የሕክምናና የሳይንስ ቃላት ሲተረጎሙ የመጀመሪያው ትርጉም እንዳይለወጥ ልዩ ጥንቃቄ ይደረጋል።

የሳይንሳዊ ሕትመቶች ዋና ርዕሶች፣ የጸሐፊዎች ስሞች፣ የማጣቀሻ መረጃዎች፣ DOI መለያዎችና ሌሎች የምርምር መለያዎች እንደ አስፈላጊነቱ በመጀመሪያው ቋንቋ ይጠበቃሉ።

በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ይዘቶች ትክክለኛነታቸውን፣ ወጥነታቸውንና የታለመላቸውን ተጠቃሚዎች ፍላጎት በመጠበቅ ይሻሻላሉ።

BOSAD ለንባብ አመቺ የፊደል አቀራረብ፣ ግልጽ የድረ-ገጽ አሰሳ፣ ትርጉም ያላቸው አገናኞች፣ በቁልፍ ሰሌዳ የመጠቀም ችሎታ እንዲሁም ለምስላዊና ለድምፅና ምስል መረጃዎች ተስማሚ አማራጮችን በማቅረብ ዲጂታል መረጃዎቹን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል።

5. የይዘት አዘገጃጀት ነፃነትና ግልጽነት

የBOSAD ሳይንሳዊና ትምህርታዊ ይዘቶች በተገቢ ማስረጃዎች፣ በባለሙያዎች የሙያ ውሳኔ እንዲሁም በBOSAD የሕዝብ ጤናና የትምህርት ዓላማዎች ላይ ተመሥርተው ይዘጋጃሉ።

የገንዘብ ድጋፍ ምንጮች፣ የጸሐፊዎች ስሞች፣ የተቋማት ግንኙነቶችና ሌሎች አስፈላጊ አስተዋፅኦዎች ከሚመለከታቸው ምርምሮች ወይም እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዘው ይመዘገባሉ።

የገንዘብ ድጋፍና የተቋማት ተሳትፎ የሳይንሳዊ ግኝቶች እንዴት እንደሚተረጎሙ ወይም የጤና መረጃዎች እንዴት እንደሚቀርቡ አይወስኑም።

ከBOSAD ሥራዎች ጋር ስለተያያዙ ድርጅቶችና ተቋማት መረጃ በ«የገንዘብ ድጋፍና ተቋማዊ ግንኙነቶች» ገጽ ላይ ቀርቧል።

የገንዘብ ድጋፍና ተቋማዊ ግንኙነቶች

6. የመረጃ ማሻሻያዎችና እርማቶች

BOSAD የሚያትማቸው መረጃዎች ትክክለኛ፣ ግልጽና ወቅታዊ ሆነው እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ክትትልና ማሻሻያ ያደርጋል።

ስህተቶችን ለማረም፣ ማብራሪያዎችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ የመረጃ ምንጮችን ለማዘመን ወይም አዳዲስ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችንና የሕክምና መመሪያዎችን ለማካተት ይዘቶች ሊሻሻሉ ይችላሉ።

አነስተኛ እርማቶች

አነስተኛ እርማቶች የፊደል ስህተቶችን፣ የጽሑፍ አቀራረብ ችግሮችን፣ የማይሠሩ አገናኞችንና የመረጃውን ዋና ትርጉም ሳይቀይሩ የሚደረጉ ማብራሪያዎችን ያካትታሉ።

ዋና ዋና የይዘት ለውጦች

ዋና ዋና የይዘት ለውጦች የመረጃውን ትርጉም፣ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን፣ የሕክምና ትርጓሜዎችን፣ የደህንነት መረጃዎችን ወይም አስፈላጊ የመረጃ ምንጮችን የሚመለከቱ ማሻሻያዎችን ያካትታሉ።

ግልጽነትን ለመጠበቅና አንባቢዎች በመረጃው ላይ የተደረጉ ለውጦችን እንዲረዱ፣ አስፈላጊ ሲሆን ከዋና ዋና ማሻሻያዎች ጋር የለውጡን ወይም የእርማቱን ምክንያት የሚገልጽ ማስታወቂያ ይቀርባል።

ስህተት ወይም ችግር ማሳወቅ

አንባቢዎች ትክክል ያልሆነ፣ ግልጽ ያልሆነ፣ ወቅታዊነቱን ያጣ ወይም የተሳሳተ ግንዛቤ ሊፈጥር የሚችል መረጃ ሲያገኙ እንዲያሳውቁን እናበረታታለን።

ለዚህ የተዘጋጀውን የBOSAD የመገናኛ ገጽ በመጠቀም፣ ካሉም ጉዳዩን የሚደግፉ መረጃዎችን በማካተት ሪፖርት ማቅረብ ይቻላል።

የሚቀርቡ ጥቆማዎች እንደ ጉዳዩ ባህሪና በቀረቡት መረጃዎች መሠረት ይገመገማሉ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ተገቢው እርማት ይደረጋል።

እርማት ይጠቁሙ

7. ምስሎች፣ ግላዊነትና ኃላፊነት የተሞላበት አቀራረብ

BOSAD ለትምህርት፣ ለምርምር መረጃ ስርጭትና የሕዝብን ግንዛቤ ለማሳደግ ፎቶግራፎችን፣ ሥዕሎችን፣ ቪዲዮዎችንና ሌሎች ምስላዊና ድምፅን ያካተቱ መረጃዎችን ይጠቀማል።

ምስላዊ መረጃዎች ከሚያብራሩት ይዘት ጋር ተዛማጅ መሆን አለባቸው። እንዲሁም በምስሎቹ ላይ የሚታዩ ሰዎችን ግላዊነት፣ ክብርና መብቶች በሚጠብቅ መንገድ መጠቀም አለባቸው።

ለማብራሪያ የሚያገለግሉ ምስሎች በእነሱ ላይ የሚታዩ ሰዎች በእውነት የBOSAD ታካሚዎች፣ የጥናት ተሳታፊዎች ወይም የተወሰነ የምርምር ቡድን አባላት እንደሆኑ የተሳሳተ ግንዛቤ መፍጠር የለባቸውም።

የግለሰቦችን ማንነት ሊገልጹ የሚችሉ የሕክምና ወይም የግል መረጃዎች ተገቢው ፈቃድ ተገኝቶ ግላዊነትን የሚጠብቁ እርምጃዎች በተወሰዱበት ሁኔታ መያዝ አለባቸው።

በBOSAD ዲጂታል መድረኮች በኩል የሚላኩ መረጃዎች በድረ-ገጹ የግላዊነት ፖሊሲ መሠረት ይስተናገዳሉ።

የግላዊነት ፖሊሲ

8. የትምህርታዊ መረጃና የሕክምና እንክብካቤ ልዩነት

BOSAD ለሕዝብ የሚያቀርባቸው የጤና መረጃዎች ለትምህርት፣ ለግንዛቤ ማሳደግና ሰዎች ስለ ጤናቸው በቂ መረጃ ላይ ተመሥርተው እንዲወያዩ ለማገዝ የተዘጋጁ ናቸው።

እነዚህ መረጃዎች ለግለሰብ የተለየ የበሽታ ምርመራ ውጤት ወይም የሕክምና ዕቅድ አይሰጡም። እንዲሁም ብቃት ባለው የጤና ባለሙያ የሚደረግን ምርመራና የሚሰጥን ሕክምና አይተኩም።

ስለ ጉዳት እንክብካቤ፣ ስለ ማገገም፣ ስለ ሕክምና ሂደቶችና የጤና ችግሮች የሚቀርቡ መረጃዎች የእያንዳንዱን ሰው የጤና ሁኔታና የሕክምና ፍላጎት እንዲሁም ለእንክብካቤው ኃላፊነት ያላቸውን የጤና ባለሙያዎች ምክር ከግምት በማስገባት መረዳትና መጠቀም አለባቸው።

ለጤና ባለሙያዎች የተዘጋጁ የመማሪያ መርጃዎች፣ የሕክምና ሂደቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችና ተግባራዊ የማሳያ መረጃዎች ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች የተዘጋጁ ሲሆኑ፣ ተገቢ በሆነ የሙያ ሥልጠናና የባለሙያ ክትትል ሥር መጠቀም አለባቸው።

አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ማንኛውም ሰው በአካባቢው ወደሚገኝ ተገቢ የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ወይም የጤና ተቋም በመሄድ ወዲያውኑ እርዳታ ማግኘት አለበት።

BOSADን ያግኙ

ስለ BOSAD የይዘት አዘገጃጀት መስፈርቶች፣ ስለታተሙ መረጃዎች ወይም ስለ እርማት አደራረግ ጥያቄ ካለዎት፣ እባክዎ መልዕክት ይላኩልን።

BOSADን ያግኙ